1.
ዛሬ የከበበኝ በዙሪያዬ
እረፍት አልሰጥ ያለው ለአእምሮዬ
የተወሳሰበው ተበጣጥሶ
እዘምራለሁ ምርኮዬ ተመልሶ
ዛሬ መስቀል ሆኖ የከበደኝ
የማመስገን መብቴን የነፈገኝ
ሲናድ ሲፈራርስ መሠረቱ
አየዋለሁ በዐይኔ በብረቱ
ለእኔስ ምንም ቢሆን ቤትህ ይሻለኛል
ባለቅስም እንባዬ ምግብ ይሆነኛል
ተመችቶኝ ይሁን ወይም ተቸግሬ
ጌታ መስቀልህ ስር ይሁን መቃብሬ (2)
2.
ይሆናል ያልኩት አለመሆኑ
እምነቴ ቀን በቀን መፈተኑ
አስመርሮኝ ከቤትህ ብወጣ
ምን ቸገረህ አንተ ሰው አላጣህ
ጉዳቱ ለእኔው ነው ዞሮ ዞሮ
በዓለም እጅ መጣል ተወርውሮ
መውጣት በማይቻል ስምጥ ሸለቆ
ጠውልጐ መቅረት ነው እዚያው ደርቆ
3.
አንተ ዝም ብትል ለአላማህ
ጥያቄዬን ሰምተህ እንዳልሰማህ
አንድ ቀን እንባዬን ታስባለህ
በደስታ ልቤን ታስረሳለህ
የጠላቴን እራስ ትመታለህ
የረቱኝን ሁሉ ትረታለህ
የተበላሸውን ታበጃለህ
ለባርያህም ድልን ታውጃለህ