1.
በወጀብ ባውሎ ንፋስ ውስጥ ስንጐሽም ስንገፋ
ደረሰልን የእኛ ጌታ ታዳጊው የእሥራኤል ተስፋ
ሞገዱንም ገሰጸልን ማዕበሉንም ጸጥ አረገው
እልል እንበል እናመስግን ዛሬ የደስታችን ቀን ነው።
የምሥጋና ቀን ነው ለእኛ ዛሬ
የአዲስ ቅኔ የዝማሬ
ኑ እናመስግን ጌታ አምላካችንን
ሰርቶልናልና ሥራችንን (2)
2.
ከአቅማችን በላይ ከብዶን የሚረዳን ወገን አጥተን
ረዴታችን መጣልን የያዕቆብ አምላክ አሰበን
በአዲስ ቅኔ በዝማሬ በከበሮ እናስተጋባ
ሥራችንን ሠርቶልናል ምሥጋናችንን እናግባ።
3.
ቁጣው ነዶ በላያችን የተመኘው ለሞታችን
በቆፈረው ጉድጓድ ገባ አመጸኛው ጠላታችን
ስለዚህ እንውጣ ዛሬ በእልልታ እየዘመርን
እስትንፋስ ያላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እናመስግን።