እግዚአብሔር ሲረዳ ከሰማያት ወርዶ
በደልን ሲያስወግድ በቅንነት ፈርዶ
አላያችሁም ወይ መጥመዱ ሲሰበር
ምርኮኛው ተለቆ ማዳኑን ሲናገር
1.
በሕይወት ጐዳና ፈተና ቢበዛም
ጌታን እየጠራ ንጹህ ሰው አይጠፋም
እጄን ያዘኝ ብሎ ሲጮህ ይሰማዋል
ከረግረግ አውጥቶ በድል ይመራዋል።
2.
ችግረኛውን ሊውጥ ጠላት ሲገዳደር
በሚያስፈራራ ቃል በትዕቢት ሲናገር
ደርሶ የሚታደግ እግዚአብሔር ብቻ ነው
በሰው መታመን ግን የከንቱ ከንቱ ነው።
3.
ያለውን ተነጥቆ ሁሉን ነገር አጥቶ
በአጠገቡ የሚቆም ጌታው ብቻ ቀርቶ
በእንግድነት አገር ተገፍቶ ለሚያልፈው
ተስፋው መሠረቱ አምላኩ ብቻ ነው።
4.
የቅዱሳን ረድኤት ከሰማይ ይመጣል
ዘመናትን ቆጥሮ ጌታ ይመለሳል
የልጆቹን እንባ ከአይናቸው ያብሳል
ክብርና ምሥጋና ለስሙ ይሆናል።