1.
እግዚአብሔር አምላክ እኛን በመውደዱ
በዘለዓለም ምክሩ በበጐ ፈቃዱ
ውድ ልጁን ልኮ ከኃጥያት አዳነን
ገንዘቡም ሊያደርገን ዋጋ ከፍሎ ዋጀን
መድኃኒታችን ከአመፅ ተቤዠን
በደሙ አንጽቶ ለእራሱ ቀደሰን
የመንግሥቱም ወራሽ ወገን አደረገን
2.
የናዝሬቱ ኢየሱስ በፀጋ ተሞልቶ
የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ተቀብቶ
ሕዝቡን እየፈታ ዞረ እየፈወሰ
የዲያቢሎስንም ሥራ እያፈረሰ
የአምላካችን ማዳን የታዳጊነቱ
ዝናውም ሲነገር የኃያልነቱ
ጠላት ተቀጥፈዋል ነደደ መኣቱ።
3.
ሊቀ ካህናቱ የአይሁድም አለቆች
ሄሮድስ ጲላጦስ የዚያ ዘመን ዳኞች
ቢመረምሩትም በደል አጡበት
ጻድቅ ነው ጌታችን የለውም ስህተት
ነውርና እድፍ ነቀፋ የሌለው
መስዋዕት በመሆን ስለ እኛ የሞተው
ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን የሱስ ነው
4.
ጀርባውን በጅራፍ በእጅጉ ገርፈው
እጆቹን እግሮቹን በምስማር ቸንክረው
በመስቀል አዋሉት እንደ በደለኛ
የነፍሳቸውን ዋስ ያን ታማኝ እረኛ
የሚያደርጉትን ባለማወቃቸው
አብ ኃጢአታቸውን እንዳይዝባቸው
እርሱ ግን ማለደ ይቅር እንዲላቸው
5.
መተላለፋችን ተግሳጽ ቅጣታችን
ደዌ ህመማችን ስቃይ መከራችን
በምህረቱ አዋጅ ወደቀ እዳችን
በኢየሱስ ቤዛነት ተሻረ ሞታችን
በእርሱ ስላገኘን ሰላምና እርካታ
ሃዘንን በደስታ ዋይታን በእልልታ
ስለ ለወጠልን ይክበር የእኛ ጌታ
በአንተ ስላገኘን ሰላምና እርካታ
ሃዘንን በደስታ ዋይታን በእልልታ
ስለ ስለወጥክልን ክበር የእኛ ጌታ