1.
እግሮችም የሉኝም ፊትህ የምቆምበት
ዓይኖችም የሉኝም አንተን የማይበት
የጠራኸኝ አምላክ ውርደቴን ተመልከት
ከገባሁበት ማጥ አውጣኝ በአንተ ምህረት
ስብራቴ የማይፈወስ ይመስላል
መደኃኒቴ አንተ ግን ምን ይሳንሃል
ምህረትህ ካለ ማጉረምረም ምን ይጠቅመኛል
በእጅህ ውስጥ መውደቅ ኦ እጅግ ይሻለኛል
2.
ከአንተ የተሰወረ ምን አለ ጌታ ሆይ
ፍፁም ሳይገለጽ ተደብቆ የሚቆይ
የልቤ መርማሪ የእኔ ውስጥ አዋቂ
ጉድለቴን ይቅር በል የነፍሴ ጠባቂ
3.
ምንም ቸር ብትሆን በአንተ አይዘበትም
ጉዴን ለመሸፈን ምክንያት አላቀርብም
ያው ከነበደሌ ራሴን ሰጥቻለሁ
ምረህ ተቀበለኝ ቃልህን ጥሻለሁ
4.
ምንም እንኳን ዛሬ ሃፍረት ቢሸፍነኝ
ፊትህን ለማየት ከቶ ቢያዳግተኝ
በተስፋ ዝም ብዬ ቀኔን ጠብቃለሁ
በድል ልታድሰኝ እንደምትችል አምናለሁ